የብር የመግዛት አቅም በየአመቱ ከ17–21% ሊዳከም እንደሚችል ተጠቆመ፡፡
አማን ይኹን በአለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ገፋፊነትና በኢትዮጵያ መንግስት ይሁንታ እተፈፀመ ባለው የብርን የመግዛት አቅም የማዳከም ስራ ምክንያት አንድ የአሜሪካ ዶላር የፈረንጆቹ 2021 ሲያልቅ በባንኮች የሚሸጥበት ተመን 46.97 ሊሆን የሚችል ሲሆን፣ በ2022፣ 2023ና 2024 መጨረሻዎች ላይ ደግሞ የአንድ ዶላር ምንዛሬ ብር 53.72፣ ብር 58.23ና ብር 64.84 እንደሚሆን ከስታንዳርድ ቻርተርድ ባንክ ይፋዊና ገለልተኛ በሆነ መንገድ አልተሰራም ባለው ጥናት ላይ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ከ2024 በኋላ ደግሞ የምንዛሬ ተመኑን በገበያ የሚወሰን እንዲሆን መንግስት ከአለማቀፉ የገንዘብ ድርጅርት ጋር ቀድሞ እንደተስማሙ ይታወቃል፡፡
የብርን የመግዛት አቅም ማዳከም ዋና አላማው ወደውጪ የሚላክን ምርት ለመጨመርና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ እንደሆነ በተደጋጋሚ ተነግሯል፡፡ ይሁን እንጂ መንግስት ይህን የፖሊሲ እርምጃ ካሁን በፊት ለሰባት ጊዜ ሞክሮት ምንም አይነት ተጨባጭ ለውጥ እንዳላመጣ ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ የውጪ ንግድ ባለበት የሚንፏቀቀው ከሐገር ውስጥ ፍጆታ የሚተርፍ በቂ ምርት ስለማናመርት ነው፡፡ ሐገር ውስጥ ከፍተኛ የምርት እጥረት ስላለ ጉድለቱን ለመሙላት በቀላሉ ልናመርታቸው የምንችላቸውን ሽንኩርትና ምስር ሳይቀር ከውጭ በማስገባት ሲሸፈን ቆይቷል፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት አስር አመታት በየአመቱ በአማካኝ ሶስት ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን ወደ ውጪ ስትልክ የነበረ ሲሆን፤ በምትኩ 15 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን ስታስገባ ቆይታለች፡፡ ይህም አገሪቱን ለከፍተኛ የንግድ ሚዛን ጉድለት ያጋለጠ ከመሆኑም ባሻገር የሐገር ውስጥ ገበያው ለከፍተኛ የዋጋ ንረት የተጋለጠ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
ከውጭ የሚገባን ምርት (በተለይም የግብርና ምርትን) ለመተካት፣ እንደዚሁም ወደውጪ የሚላክ ምርትን ለማሳደግ ከተፈለገ፣ ሰባት ጊዜ ተሞክሮ ውጤት ያላመጣን መፍትሄ ከመተግበር አዲስ የፖሊሲ እሳቤና አሰራር መከተል አስፈላጊ ነው፡፡ የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት ያኮላሹ ዘመንጠገን የመንግስት የተሳሳቱ ፖሊሲዎችን አስወግዶ ከሐገራዊ ሁኔታዎች ጋር የተጣጣመ፣ አለም ዓቀፍ ተሞክሮዎችንም ከግምት ውስጥ ያስገባ አዲስ ፖሊሲ መከተል ግድ ይላል፡፡
በኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት እየገቱ ከሚገኙ የተሳሳቱ ፖሊሲዎች አንዱ የመሬት ስሪቱ ነው፡፡ የመሬት ዋና ፋይዳ ኢኮኖሚያዊ ሆኖ ሳለ፣ ኢህአዴግ መሬትን ዋነኛ የፖለቲካ መሳሪያ በማድረግ አርሶና አርብቶአደሩን ማኅበረሰብ በመሬት ምክንያት የሥርዓቱ ጥገኛ አድርጓል፡፡ አርሶአደሩ በተለይ ከመንግስት ፈቃድ የወጣ እንደሆነ የስልጣን መወጣጫችን ይናዳል በሚል የጠባብ ቡድን ፍላጎት መሬት ኢኮኖሚያዊ አበርክቶው ውስን እንዲሆን ተደርጓል፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ መሬት ሙሉ የምርት ኃይልነት (factors of production) ሚናውን እንዳይጫወት በህገመንግስት ታስሮ የሐገሪቱ የምጣኔ ኃብትና ኢንቨስትመንት እድገት ተገቶ ይገኛል፡፡
በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ ግብርና ቁጥሩ በፍጥነት እየጨመረ ለመጣው ህዝብ በቂ ቀለብ፣ ላሉን ውስን ኢንዱስትሪዎች በቂ ጥሬ እቃና፤ ለወጪ ንግድ በአይነት፣ በጥራትና በብዛት የተሻሉ ምርቶችን ማቅረብ ስንችል፤ ጭራሽ በየአመቶ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ጥሬ የግብርና ምርቶችን፣ እንደዚሁም ከሶስት ቢሊዮን አምስት ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ የተቀነባበሩ የግብርና ውጤቶችን ከውጭ እናስገባለን፡፡ ይህ አገሪቱን ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና እዳ የዳረጋት ከመሆኑም ባሻገር፣ ሥራ የሌለለው ወጣት በአስር ሚሊዮኖች በሚቆጠርበት ሐገር እየኖርን በውጭ ለሚገኙ ፋብሪካዎች የሥራ እድል እየፈጠርን እንገኛለን፡፡
የግብርናውን ዘርፍ ቀፍድደው ከያዙት ምክንያቶች ሌላው የሠው ኃይል ልማት ጉዳይ ነው። በአሁኑ ሠዓት ከፌደራል እስከ ወረዳ ድረስ ያሉ ግብርናን የሚመሩት ካድሬ አመራሮች ናቸው። በአጠቃላይ የዘርፉ አመራሮች ወደ 80% የሚጠጉት ከግብርና ጋር የሚቀራረብ የትምህርት ዝግጅት ያላቸውም፡፡
ሌላው የዘርፉ ችግር የገንዘብ አቅርቦት ነው፤ ግብርናው ለአገራዊ ጥቅል ምርት ወደ 40% የሚጠጋ፣ ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ከ70% በላይ፣ ለሥራ ቅጥር ደግሞ ወደ 80% የሚጠጋ አስተዋፆ እያበረከተ፣ መንግስት የሚመድብለት በጀት ከ10% አይበልጥም፤ በተመሳሳይ በዚህ አመት ለመጀመሪያ ጊዜ ባንኮች ከሚያበድሩት ገንዘብ እስከ 5% ድረስ ለግብርና እንዲሆን በመደረጉ የግብርናው ዘርፍ ላይ አቢዮት እየተቀጣጠለ ነው ሲሉ ምክትል የገንዘብ ሚኒስሩ ዶ/ር እዮብ ተካልኝ በግብርና፣ የገጠር ልማት፣ የመሬት ፖሊሲና የምግብ ዋስትና ጉዳዮች ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲከራክሩ ተናግረዋል፡፡ ይህ ንግግራቸው መሬት ካለው እውነታ ጋር እንደማይጣጣም እሳቸው ራሳቸው መንስክር ናቸው፡፡
ሌላው ችግር የግብርና ግብዓት ገበያ በሞኖፖል በመንግስትና የፓርቲ ድርጅቶች የተያዘ መሆኑ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በገበያ ዋጋ ከ90 ብር በታች የሚሸጡ ምርቶችን እስከ 450 ብር ለአርሶአደሩ እየቀረቡ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት የዘርፉ ማነቆዎች ላይ የተደረገ ምክክር ላይ በግል ባለሃብቶች ተነስቷል፡፡
የግብርና ገበያ ልማት ሥራን ከኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ጋር አቀናጅቶ አለመስራት በበቂ በተመረተበት አካባቢ ያለን ምርት ለሸማቹ የማቅረብ ከፍተኛ ውስንነት እንዲከሰት እያደረገው እንደሆነ ሌላው የዘርፉ ችግር ነው፡፡
ስለዚህ የውጪ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ ተብሎ የማይሰራና ሰባት ጊዜ ተሞክሮ የከሸፈን መፍትሔ ለመተግበር ከመረባረብ፣ ምርትና ምርታማነት እንዳያድግ ያደረጉትን ዘመን-ጠገብ የዘርፉ ችግሮች መፍታቱ የተሻለ ነው፡፡